የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ በየካ ክፍለ ከተማ የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቀዋል ።
በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት ተጀምረው ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና የጥራት ደረጃቸው ተጠብቆ እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል ።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ትምህርት ቤቶች ፣ ጤና ጣቢያዎች ፣ መንገዶችና የጥቃቅንና አነስተኛ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች ተመርቀዋል ።
አስተዳደሩ ያስመረቃቸው የልማት ተቋማቱ የመብራት ፣ የውስጥ መንገዶችና የውሃ አገልግሎቶች እንዲሟሉላቸው ከተደረገ በኋላ መመረቃቸውን ተገልጿል ።
ከዚህ በፊት የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በፍጥነት የማጠናቀቅና አዲስ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል ።