የኦሮሞ አባገዳዎች የበርበራን ወደብ ጎበኙ

የኦሮሞ አባገዳዎች በትላንትናው ዕለት በሶማሌላንድ የበርበራን ወደብ ጎብኝተዋል፡፡

አባገዳዎቹ ወደቡን በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ለማገዝ የበርበራ ወደብ ጉልህ ድረሻ ይኖረዋል።   

ወደቡ በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ንግድ ከማቀላጠፉ ባሻገር የህገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ እገዛ እንደሚኖረው አባገዳዎቹ ገልጸዋል ፡፡                      

ወደቡን የኢትዮጵያ፣ ሶማሌላንድና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ 442 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመመደብ ለማልማት ቀደም ሲል የሶስትዮሽ ፊርማ ያኖሩ ሲሆን ግንባታውም እኤአ  በ2019 የመጀመሪያ ወር አጋማሽ ላይ ይጀመራል ተብሏል፡፡

ሁለት ዓመታትን የሚፈጀው ግንባታ ሲጠናቀቅ አሁን ላይ ያለውን በወር ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ ኮንቴይነር የማስተናገድ አቅም ወደ 400 ሺህ ከፍ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ በወደቡ ላይ የ19 በመቶ ድርሻ ሲኖራት ሶማሌላንድና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በቅደም ተከተል የ30 እና 51 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል።

ወደቡን ከወጪና ገቢ ንግድ በተጨማሪ ለቱሪዝም መስህብነት ለማዋል መታቀዱንም መረጃዎች አመልክቷል።