በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 12ሺ ዶላርና 2 መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ሥር ዋለ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 12 ሺ የአሜሪካ ዶላር እና 2 መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል የሥራ ሂደት  ምክትል ኢንስፔክተር ደረጄ ኢታና በቁጥጥር
ሥር የዋለው ህገወጥ ገንዘብ መነሻው ደቡብ ሱዳን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ አገር ገንዘቡ ጋር 2 መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብርም በጥቁር ገበያ ሊመነዘር ሲል ከተጠርጣሪው ግለሰብ ጋር አሶሳ ከተማ ላይ በቁጥጥር ሥር ውሏል ብለዋል።

ህገ-ወጥ ገንዘቡና ተጠርጣሪው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ነው፡፡

በተጨማሪም ከህገወጥ ገንዘቡ ጋር አንድ ሽጉጥ ከአራት ፍሬ ጥይት ጋር መያዙን ያስታወቀው ምክትል ኢንስፔክተር ደረጄ በግለሰቡ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡(ምንጭ: ኢቲቪ)