ከ33 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላርና 6 ሺ 500 የሳውዲ ሪያል በቦሌ ኤርፖርት በኩል ወደ ዱባይ ሊወጣ ሲል ተያዘ

በቦሌ ኤርፖርት በኩል አድርጎ ወደ ዱባይ ሊወጣ የነበረ 33 ሺ 250 የአሜሪካ ዶላር እና 6 ሺ 500 የሳውዲ ሪያል በአልሙኒየም ወረቀት ተጠቅልሎ ሊወጣ ሲል ትናንት ከቀኑ 7 ሰዓት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡

ገንዘቡ በቀጥጥር ስር የዋለው በጉምሩክ ሰራተኞች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ መሆኑን በገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ህገ ወጥ ገንዘቡን ይዛ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ተጠርጣሪ መቅደስ ጽጌ የተባለችው መንገደኛ በቁጥጥር ስር ውላ አስፈላጊው የማጣራት ስራም እየተሰራ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ታህሳስ 10፤2011 ዓ.ም በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 41 ሺህ 693 የአሜሪካ ዶላር በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል፡፡ 

መሰል ህገ ወጥ ድርጊትን ለመከላከል ኮሚሽኑ ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጾ ህብረተሰቡ ይህንን መሰል ድርጊት ሲመለከት ለኮሚሽኑ ጥቆማ በማቅረብ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡