በወሊሶ ከተማ 80 ኩንታል ህገ ወጥ ቡና ተያዘ

ከጅማ ዞን ወደ አዲስ አባባ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓዝ የነበረ 80 ኩንታል ቡና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ሲደርስ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወሊሶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዢን ኃላፊ ኮማንደር ከበደ በዳዳ ለኢዜአ እንደገለጹት ቡናው የታየዘው የከተማው ህብረተሰብ ለፖሊስ በሰጠው  ጥቆማ  ነው።

ቡናው ትናንት እኩለ ሌሊት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 00913 አ.አ. በሆነ ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሸከርካሪ ተጭኖ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ በወሊሶ ከተማ ዩኒቨርሲቲ ጀርባ አካባቢ መያዙንም አመልክተዋል፡፡

ቡናውን ህገወጥ ሊያደርገው የቻለው ያለ ፈቃድ አሽከርካሪው ከላይ በቆሎ በመጫን ከስር ህገ ወጥ ቡና ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ለማሳለፍ በመሞከሩ ነው፡፡  

ኮማንደር ከበደ ” ፖሊስ አሽከርካሪው ለጊዜው ቢሰወርም ረዳቱን በህግ ጥላ ስር በማዋል ተገቢውን ምርመራ እያካሄደ ነው”ብለዋል ።

የተያዘው ቡናም ከ640 ሺህ ብር በላይ መገመቱንም ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ ህገ ወጥ ድርጊትን ለመከላከል እያደረገ ያለው ተሳትፎ እንዲቀጥልበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ምንጭ ፡ ኢዜአ