የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚዉል የ11 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማጠናቀቂያ የሚዉል የ11 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደርጓል፡፡

እነዚህ ፓርኮች በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ከመደበላቸው በጀት ባሻገር ለግንባታቸው ማጠናቀቂያ እንደሚዉሉም ተገልጿል፡፡

የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚአብሄር እና በአራቱ ክልሎች የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስሪ ፓርኮች ስራ አስፈጻሚዎች መካከል ተፈጽሟል፡፡

ሚኒስትሯ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት እያንዳንዱ ክልሎች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድርሻ የሚኖራቸው ሲሆን ክልሎቹም በጀቱን ለታለመለት አላማ በመጠቀም የፓርኮቹን  ግንባታ እንዲያፋጥኑ ጠይቀዋል፡፡

በሃገሪቱ በአጠቃላይ 17 የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ለመግባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ወ/ሮ ፈትለወርቅ ጠቁመዋል፡፡