አየር መንገዱ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖች ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹን በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን አስታውቋል።

አየር መንገዱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በትናንትናው እለት ቦይንግ 737-8 ማክስ በበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የደረሰበትን የመከስከስ አደጋ ተከትሎ መሆኑን ነው፡፡

በዚህም መሰረት የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ እስኪታወቅ ድረስ ለመንገደኞች ደህንነትና ጥንቃቄ ሲባል ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹን በሙሉ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን ገልጿል።

አየር መንገዱ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አምስት አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፥ በትናንትናው እለት የተከሰከሰውም ከአራት ወራት በፊት የተረከበው 4ኛው አውሮፕላኑ ነበር።

በተመሳሳይ ዜና ቻይናም በሀገሯ የሚገኙ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቿ በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኗም ተነግሯል።

የቻይና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የቻይናን አየር መንገዶች ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖችን ለበረራ መጠቀም እንዲያቆሙ አስታውቋል።

ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኘው አውሮፕላን ባለፉት አምስት ወራት የመከስከስ አደጋ ሲያጋጥመው የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነውም ተብሏል።

ከአምስት ወራት በፊት ላዮን ኤየር የተሰኘ የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል አውሮፕላን ለበረራ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ 189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።