የማዕድንና ነዳጅ ዘርፉን ችግሮች ሊፈታ የሚችል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ

የማዕድን ዘርፉን ችግሮች ሊፈታ የሚችል ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የማዕድን ስራዎች ምክር ቤት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ምክክር እያደረገ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ ያለውን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ አስታውቀዋል፡፡

በዘርፉ ከዚህ በፊት የተዘጋጁ መመሪያዎች ቢኖሩም ትልልቅ በሚባሉ ማዕድናት ላይ ብቻ ያተኮሩና በፖሊሲ ደረጃ ተግባራዊ አለመደረጋቸው በምክክር መድረኩ ላይ ተነስቷል።

በመድረኩ ማዕድናት በልጽገው ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ በሚችሉበት ደረጃ እየቀረቡ አለመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳነሱ ተጠቁሟል።

በዘርፉ ያለው የግንዛቤ እጥረት፣ እሴት ጨምሮ ለገበያ አለማቅረብ እንዲሁም በዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንት አናሳ መሆን በችግርነት ተነስተዋል።

ይህ መሆኑም ማዕድን በሃገራዊ ልማት ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ እንዲሄድ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ እየተዘጋጀ ያለው ረቂቅ ፖሊሲም የዘርፉን ችግሮች በመቅረፍ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ፣ የስራ እድል የመፍጠርና ባለሃብቶችን የማበረታታት አላማ እንዳለው በምክክር መድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የምክክር መድረኩ ለፖሊሲው ግብዓት ማሰባሰቢያ ሲሆን ረቂቅ ፖሊሲው ለሚቀጥሉት 20 አመታት እንዲያገለግል ታስቦ እንደተዘጋጀም ተገልጿል፡፡