የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ተጀመረ

የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ በዛሬው እለት በይፋ ተጀመረ።

ፋብሪካው ዓባይ ኢንዱስሪያል ልማት አክሲዮን ማኅበር ለመገንባት ካቀዳቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን፥ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የሚገነባ ነው።

የፋብሪካውን ግንባታም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል አስጀምረውታል።

የፋብሪካው ግንባታ በሁለት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፥ በ28 ወራት ውስጥም የሙከራ ምርት ለማስጀመር እቅድ ተይዞለታል።

ለግንባታውም 8 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ ይደረጋል ተብሏል።

ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈም በቀን 5 ሺህ ቶን ክሊንከር እንዲሁም በዓመት 2 ነጥብ 25 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ያመርታል ተብሎም ነው የሚጠበቀው። (ምንጭ፡- ኤፍቢሲ)