ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አካሄዱ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ ከመርካቶ እና አካባቢው ግብር ከፋይ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ወቅት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ባደረጉት ንግግር በመዲናዋ በተለያየ መንገድ የሚስተዋሉና የህግ የበላይነት የሚሸረሽሩ እንዲሁም ህዝብን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ለመውሰድ ታስበውና ታቅደው የሚሰሩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ እንቅፋትና ስጋት እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም እነዚህ የከሰሩ እንቅስቃሴዎች አንድም በአጭር ጊዜ ከተማዋ ያስመዘገበቻቸውን ታላላቅ ውጤቶች ለማኮሰስ በሌላ በኩል ደግሞ በብዙዎች መሰዋዕትነት የተገኘውን የለውጥ ምዕራፍ ለመቀልበስና ሀገራችንን ለመበታተን ያለሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ስለሆነም የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል ህብረተሰቡ እነዚህንና መሰል ተግባራት የሚያራምዱ አላካትን አምርሮ ሊታገላቸው የሚገባ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የከተማ አስተዳደሩም የህግ የበላይነትን በሚጥሱ መሰል እንቅስቃሴዎች የሚገለፁ ድርጊቶችን ያለምህረት እንደሚታገላቸው እና ድርጊቱን ለማስቆም ህጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በዛሬው ዕለት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ድንገተኛ የስራ ምልከታ ማድረጋቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤታ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በምልከታቸውም በክፍለ ከተማው ስር ባሉ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን የጎበኙ ሲሆን፥ ከተጠቃሚዎች ፣ ከክፍለ ከተማው አመራሮች እና ሰራተኞች ጋርም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ነው የተገለፀው።