የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚችል ጠንካራ መንግስት የሚፈጠረው በሀቀኛ ግብር ከፋዮች ነው – አቶ ለማ መገርሳ

የሕዝብን ጥያቄ መመለስ የሚችል እና ጠንካራ መንግስት የሚፈጠረው ሀቀኛ ግብር ከፋይ ሲፈጠር መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በኦሮሚያ ክልል ለ1 ዓመት በሚቆየው የግብር ንቅናቄ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር አድርገዋል።

አቶ ለማ ማንኛውም የልማት ጥያቄ ለመመለስ ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚስፈልግ ገልጸው፣ ሕብረተሰቡ ግዴታውን በመወጣት መብቱን መጠየቅ ይኖርበታል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ንቅናቄው የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር መሰብሰብ ያለበት ገቢ እንዲሰበሰብ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ላይ በተሰራው የሪፎርም ስራ ከ10 ዓመት በፊት ከ600 ሚሊየን ብር የማይበልጠው ገቢ በአሁን ወቅት 19 ቢሊየን ብር መድረሱን አስታውቀዋል።

ሆኖም ከዚህ ገቢ አብላጫው የሚሰበሰበው ከሰራተኞች በመሆኑ ይህም ክልሉ ከሚያመነጨው ገቢ አንፃር ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ያመላከተ ነው ተብሏል።

ከግብር የሚሰበሰበውን ገቢ በማሳደግ የህዝቡን የልማት ጥያቄ በተሻለ መልኩ ምላሽ እንዲያገኝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በርብርብ ሊሰሩ እንደሚገባ ተነግሯል።

ለአንድ አመት የሚቆየው የግብር ንቅናቄ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት “ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴንም እጠይቃለው” በሚል በመሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን በስነ ስርዓቱ ላይ ከ1 ሺህ እንግዶች ተሳፈዋል።

በኦሮሚያ ክልል በ2011 ዓ.ም. በጀት ዓመት 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። (ምንጭ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ)