ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በአፍሪካ ኩባንያ መሪዎች ፎረም ላይ ለመሳተፍ ሩዋንዳ ገብተዋል

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ ስራ አስፈጻሚ መሪዎች በሚካፈሉበት ፎረም ላይ ለመሳተፍ ሩዋንዳ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስራ አስፈጻሚዎች ፎረም ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በ7ኛው የአፍሪካ ስራ አስፈጻሚዎች ፎረም የአፍሪካ ኢኮኖሚን አጀንዳቸው ያደረጉ 1 ሺህ 500 መሪዎች ይገኙበታል ተብሏል።

ፎረሙ ኪጋሊ ላይ ለሁለት ቀናት መጋቢት 16 እና 17 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

ፎረሙ በአፍሪካውያን የእርስ በእርስ ግብይት፣ ኢንቨስትመንት፣ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ውህደት እንዲሁም የግል ሴክተሩን ማጎልበት፣ ምቹ ፖሊሲዎችን መቅረጽና ዘላቂና የተረጋጋ ንግድ ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው የተባለው።

የአፍሪካ ስራ አስፈጻሚዎች ፎረም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2012 ላይ የተጀመረ ሲሆን፣ በየዓመቱ በአህጉሪቱ ንግድ ላይ ያተኮረ ፎረሞችን ያካሂዳል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን እንደሚደግፍ ፎረሙ ገልጿል።

ለሁለት ቀናት በሚያከሄደው በዚህ ውይይት በቱሪዝም ዘርፍ፣ በፀሐይ ሃይል ዙሪያ፣ በሴቶች ተሳትፎ፣ በባንክ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።   

(ምንጭ፡-የፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት)