ከኃይሌ ጋርመንት እስከ ጀሞ 3 እየተገነባ ያለው መንገድ የወሰን ማስከበር ችግር እንደገጠመው ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ ከኃይሌ ጋርመንት እስከ ጀሞ 3 እየተገነባ ያለው መንገድ የወሰን ማስከበር ችግር እንደገጠመው ተገለጸ፡፡

በ550 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እየተገነባ ያለው መንገድ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሲሆነው፣ አፈፃፀሙ መድረስ ከነበረበት 50 በመቶ አሁን ላይ 29 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ለዚህ ደግሞ በመንገድ ግንባታው አካባቢ ሶስት ቦታዎች ላይ ያሉ 200 የሚሆኑ ቤቶች ባለመፍረሳቸው ግንባታውን እንዲጓተት አድርጓል ነው የተባለው፡፡

የመንገድ ግንባታውን የሚያከናወነው ተቋራጭና አማካሪ ድርጅቱ የወሰን ችግር ካለባቸው ቦታዎች ውጪ ያሉትን መንገዶች በአግባቡ ማከናወን ቢችልም ቤቶችና ነዋሪዎች ባለመነሳታቸው ምክንያት ግንባታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጓቶብኛል ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል በበኩላቸው ለተነሺዎቹ አስፈላጊውን ካሳ መሰጠቱን ተናግረዋል፤ ይሁን እንጂ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ለነዋሪዎቹ ተለዋጭ ቦታ ስላልተሰጣቸውና ከቦታው ባለመነሳታቸው ችግሩን ለመፍታት እንዳልተቻለ አክለው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ክፍለ ከተማው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ችግሩን በፍጥነት እንዲፈታም ባለስልጣኑ መጠየቁን ታውቋል፡፡