የንግድና ኢንቨስትመንት ሪፎርሞች ኢንቨስተሮችን እየሳቡ ነው — የኢንቨስትመንት ኮሚሽን

በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የአሰራር ሪፎርሞች ከወዲሁ ኢንቨስተሮችን እየሳቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

በ140 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባውና በቅርቡ ሥራ የጀመረው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ ለሙሉ በባለኃብቶች መያዙንም አክሏል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ አስር የሚሆኑ አሰልቺ አሰራሮች ተለይተው ማሻሻያ እየተደረገባቸው ነው።

የኢንቨስትመንት ህጉን ለማሻሻል ግብረኃይል እንደተቋቋመም ጨምረው ገልጸዋል።

እየተከናወኑ ያሉት የማሻሻያ ተግባራት የተለያዩ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸውን መፍሰሳቸውን ፍላጎት እንዲያሳድሩ አድርጓል ነው ያሉት አቶ አበበ።

ከኢሺያ አገራት በተጨማሪ ባልተለመደ መልኩ በርካታ የምዕራባዊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት ማሳደራቸውን በአስረጂነት አንስተዋል።

በተጨማሪ የተለያዩ ባለሃብቶች አዲስ በተመረቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አቶ አበበ ገልጸዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምእራፍ 19 የማምረቻ ሼዶች ያሉት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በባለኃብቶች ተይዘዋል። 

የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ደግሞ 75 በመቶ በላይ በባለሃብቶች መያዛቸውን ለአብነት አንስተዋል። 

ባለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 75 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች። 

የቻይና፣ ህንድና ቱርክ ባለኃብቶች በተጠቀሰው ዓመት በኢትዮጵያ መዋእለነዋያቸውን ካፈሰሱት መካከል በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ጊዜ  ውስጥ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይስተዋል በነበረው የፓለቲካዊ አለመረጋጋት የኢንቨስትመንት ፍሰቱን እንደጎዳው ይነገራል። (ምንጭ፡- ኢዜአ)