የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የንግድና ፋይናንስ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የንግድና ፋይናንስ ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ የዘርፉ ተዋናዮች እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፡፡

በጉባኤው ለመንግስት፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለንግዱ ማህበረሰብ የሚጠቅሙ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ በማበረታት በሀገር ኢኮኖሚና በአህጉርዓቀፍ ደረጃ በተያዘው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ሚናቸው የጎላ እንዲሆን ለማስቻል የፖሊሲ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችን አድርጋ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሾመ ታፈሰ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሽንቁጥ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ለውጥ ከመጣ ወዲህ በኢኮኖሚ ዘርፍ በተወሰደው እርምጃ የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለ በጉባኤው ላይ አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት አባል አገራትና በነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የታቀፉ ሀገራት በፖሊሲዎቹም በመደጋገፍ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ትስስርን ማጠናከር እንዳለባቸው በጉባኤው ላይ የተገኙት የአፍሪካ ህብረት የንግድ ኮሚሽነር አልበርት ሙቼንጋ አሳስበዋል፡፡ የግል ባለሀብቶችም በዘርፉ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡