የማሌዢያው ኩባንያ በኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ምርት ላይ ሊሰማራ ነው

ጎልደን አፍሪካ የተባለ የማሌዢያ ኩባንያ በኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ዘርፍ ኢንቬስት ሊያደርግ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር በዘርፉ ባለው የኢንቬስትመንት እድል ዙሪያ ለኩባንያው ሀላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በአገሪቱ ያለው የምግብ ዘይት ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም 90 በመቶ የሚደርሰው ምርት የሚገኘው ከውጭ አገራት በግዢ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በከተማም ሆነ በገጠር የህዝቡ የኑሮ ደረጃ በተሻሻለ ቁጥር የሸማቹ የምግብ ዘይት ፍላጎትና ምርጫ ከፍ ስለሚል በዘርፉ መሰማራት አዋጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከውጭ አገራት የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለሚያመርቱ ኢንቬስተሮች አገሪቱ ጠንካራ የታሪፍ ጥበቃ እንደምታደርግ ሚንስትሯ አብራርተዋል፡፡

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፎድ ሀይል በበኩላቸው በኢትዮጵያ ምቹ የኢንቬስትመንት እድሎች በመኖራቸው በምግብ ዘይት ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ስራውን እንደሚጀምርና ለ1 ሺህ 500 ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡

(ምንጭ፦ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር)