238 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በአሸባሪው ሕወሓት ዘረፋና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል

አቤ ሳኖ

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በ238 የባንኩ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በባንኩ ሰራተኛች ላይ ግድያ እንዲሁም በተቋሙ ላይ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።

አሸባሪው ኃይል በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት ዲስትሪክት ስር ባሉ 238 የባንኩ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል ነው ያሉት።

ከአሸባሪው ወረራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የባንኩ ቅርንጫፎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አረጋግጠናል ያሉት የባንኩ ፕሬዝዳንት በመቐሌ የሚገኙት 61 እና በሽሬ 59 የባንኩ ቅርንጫፎች ያሉበት ሁኔታ እስካሁን አይታወቅም ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ገንዘብ፣ ኮምፒውተር፣ ጀነሬተሮችና ሌሎች ንብረቶችን በመዝረፍ የኤቲኤም ማሽኖችን በመስበርና በማውደም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አብራርተዋል።

ከወራሪው ነፃ የወጡ አካባቢዎች በባንኩ ቅርንጫፎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር ለማወቅና ዳግም ስራ ለማስጀመር የጥናት ቡድን መሰማራቱን ገልጸዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ በባንኩ ቅርንጫፎች ላይ የሰነድና የንብረት ውድመት ቢደርስም የደንበኞች መረጃ ግን ሙሉ በሙሉ ማዕከል ላይ ስለሚገኝ ደንበኞች “መረጃዬ ይጠፋል” የሚል ምንም አይነት ስጋት ሊኖራቸው አይገባም።

ከአሸባሪው ሕወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች እስካሁን 12 የባንኩ ቅርንጫፎች ዳግም ስራ መጀመራቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ደግሞ 30 የሚሆኑትን ስራ ለማስጀመር ዝግጅት ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።