የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ጋር አራት የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራረመ

ከቤልትና ሮድ ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ጋር አራት የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርሟል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በቻይና መዲና ቤጂንግ ለሁለተኛው ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የቤልት ኤንድ ሮድ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ላይ እየተካፈሉ ይገኛል።

ከዚህ ዓለም አቀፋዊ የትብብር ጉባኤው ጎን ለጎን ነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር የኢንቨስትመንት ስምምነት የተፈራረመው፡፡

ከነዚህ ኩባንያዎች መካከል ቴይሰን ቡድንና ግሪን ዳይመንድ የተባለ ኩባንያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ እስከ 1ሚሊየን ቶን ወረቀት በዓመት ለማምረት የተዋዋለው የቀርከሀ ወረቀት ፋብሪካ አንዱ ነው፡፡

አሚቲ የኅትመት ስራ ድርጅት በኢትዮጵያ የማተሚያ ቤት ለመክፈት የተፈራረመ ሲሆን

ሲ ጂ ሲ. ኦ ሲ ቡድን በዓመት እስከ 300 ሺህ ከብትና 3 ሚሊዮን በጎች ለገበያ የሚያቀርብ የቁም ከብትና ሥጋ ማሰናጃ ቄራ ሌላኛው ነው፡፡

አራተኛው ዜንዴ የሕክምና ውጤቶች ማምረቻ በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሕክምና መገልገያዎች ማምረቻ፣ የቁስል ማከሚያ፣ የቀዶ ጥገና ማካሄጃ፣ የፕሬሸር ሕክምናና ቋሚ መገልገያዎችን የሚያመርት ኩባኒያ ነው፡፡/የጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት/