ለሸገር ገበታ እስካሁን 34 ድርጅቶች ተሳታፊ መሆናቸው ተገለፀ

ሸገርን ለማስዋብ በሚል ይፋ በሆነው የእራት መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ እስካሁን 34 ድርጅቶችና ኩባንያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አጋፋሪነት የሚዘጋጀው ይኸው የእራት መርሃ ግብር ጊዜው መቃረቡንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዚህ እራት ላይ ለመታደምና የፕሮጀክቱ አካል ለመሆን ባንኮች፣ ፋብሪካዎች፣ የንግድ ተቋማትና የግንባታ ድርጅቶች ግንባር ቀደም ተሳታዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ለሸገር የማስዋብ ፕሮጀክት በአንድ ግለሰብ የተጠየቀውን የ5 ሚሊየን ብር ክፍያ ተሳታፊዎቹ በባንክ ያስገቡበትን ደረሰኝ ለማስረጃነት እንዲልኩም ተጠይቀዋል፡፡

ክፍያውን የፈፀሙ ተቋማት ጊዜው በተቃረበው የሸገር ገበታ ላይ ይታደማሉ፣ በፕሮጀክቱ ሂደትም የድርጅቶቹ አስተዋፅኦ ተካቶ እውን እንደሚሆን መረጃው ያመለክታል፡፡

በዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ሸገርን በማስዋብ ሂደት ተሳታፊ ለሆኑ ድርጅቶችና ኩባንያዎችም መንግስት ምስጋና አቅርቧል፡፡