የሱዳን ባለሃብቶች ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎበኙ

የሱዳን ባለሃብቶች የቦሌ ለሚን እና የቂሊንጦን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ በኢትዮ-ሱዳን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ለመሳተፍ የመጡ ሲሆን በጉብኝታቸውም ወቅት በፓርኮቹ አመራሮች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በፓርኮቹ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ባለሃብቶቹ ገልጸው በቀጣይም ፋብሪካዎች የመገንባት ሃሳብ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ያከናወነችው ተግባር ስኬታማነት  የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ እየሳበ እንዲመጣ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገሪቱ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡