ከአዲሱ የኪራይ ዋጋ ተመን ጋር ተያይዞ የቀረበዉ ቅሬታ መፈታቱን ኮርፖሬሽኑ ገለፀ

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከአዲሱ ኪራይ ዋጋ ተመን ጋር ተያይዞ ቅሬታ አቅርበዉ የነበሩ 2 ሺህ ጉዳዮችን መፍታቱን ገለጸ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል እና የኮርፖሬቱ የስራ ሃላፊዎች ለዋልታ እንደተናገሩት የዋጋ ማስተካከያ የተደረገዉ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ከዚ የተሰበሰበዉ ገቢ ተቋሙ መልሶ ለሚገነባቸዉ ቤቶች ለመዋል ነዉ፡፡

አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ላይ ድርጅቱ ከስድስት ሺህ በላይ ያሉት ሲሆን ማስተካከያ ዋጋ ተግባራዊ ከተደረገ በኃላ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ቅሬታዎች አቅርበዉ በኮርፖሬሽኑ መፍትሄ ተስጥተዋል ነዉ ያሉት፡፡

አራት መቶ የሚደርሱ ደንበኞች በህገ-ወጥ መንገድ ቁልፍ በመግዛት ቤቶችን ይዘዉ የተገኙ ቢሆንም የፌዴራል ቤቶች ኮርፕሬሽኑ የማኔጅመንት እና የቦርድ አባላት ቤቱን የያዙት ግለሰቦች ህጋዊ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ አድርገዋል ብለዋል፡፡

የቤቶች ኮርፕሬሽን በሌላ በኩል ከዚህ በፊት በ አንድ ንግድ ዘርፍ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ሲሆን አሁን ተከራዮቹ ካቀረቡት ጥያቄ አንፃር በአንድ ቤት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች እንዲሰሩ መፈቀዱንና ሌሎች ቅሬታዎችን መፍታት መቻሉን ዋና ስራ አፈፃሚዉ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ራሳቸዉ የነጋዴ ኮሚቴ ነን የሚሉ አካላት ጉዳዩ እናስፈፅምላችኋለን፣ የተደረገዉን ጭማሪ እናስመልስላችኃለን በማለት በነፍስ ወከፍ ከ1 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ከነጋዴዎች በህገ-ወጥ መንገድ በመሰብሰብ የንግዱን ማህበረሰብ ግራ እያጋቡት ይገኛሉ ብለዋል አቶ ረሻድ፡፡ 

ኮርፖሬሽኑ እነዚህን አካላት በህግ ለመጠየቅ ዝግጅት ያጠናቀቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ራሱን ካላስፈላጊ ወጪ እንዲጠብቅ እና አሁንም ጥያቄ ካለ ወደ ኮርፖሬሽኑ መጥተዉ ጥያቄቸዉ እንዲያቀርቡ አሳስቧል፡፡