ስትሬት ግሩፕ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተሸከርካሪ መገጣጠሚያ ለመገንባት ፍላጎቱን ገለጸ

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ወታደራዊና የአደጋ ጊዜ የደህንነት ተሽከርካሪዎቸን የሚያመርተው ስትሬት ግሩፕ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተሸከርካሪ መገጣጠሚያ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ፡፡

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በወታደራዊ እና ለደህንነት አገልግሎት የሚውሉ እንዲሁም ሌሎች ሲቪል ተሽከርካሪዎችን የሚያመርተውን ስትሬት ግሩፕ ኩባንያን በጎበኙበት ወቅት ነው የኩባንያው ዋና አስተዳዳሪ ሩሴል አርኖት የተናገሩት፡፡

እንደ ኩባንያው አስተዳዳሪ ገለፃ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላት ተቀባይነት እና የድርጅታቸውን ምርት ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለመላክ ስትራቴጂያዊ ቦታ መሆኗን ገልፀዋል። ለዚህም ነው ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት ከፍተኛ ፍላጎት ያደረበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአምባሳደሩ ጉብኝትም ለኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስተዋወቅ እና ወደ ኢትዮጵያም በመምጣት መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ ለማግባባት ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል።

በጥቂት ቀናት ውስጥም ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ አንድ ልዑክ በመላክ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንደሚያጠና ነው በውይይቱ የተገለፀው።

አምባሳደሩ ከጉብኝታቸው በኋላ እንዳሉትም ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ አጥኚ ቡድን በመላክ የሚያገኘውን ውጤት መሰረት አድርጎ በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋዩን እንደሚያፈስ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።