የኤሌክትሪክ ሀይል ስርጭት በፈረቃ ሊደረግ ነው

የኤሌክትሪክ ሀይል ስርጭት በፈረቃ ሊደረግ መሆኑን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በግድቦች በቂ ውሀ ባለመኖሩ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የኃይል መቆራረጡ የተከሰተው በተለይ በጊቤ 3 የሀይል ማመንጫ ግድብ በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት የግድቡ ውሀ በመቀነሱ መሆኑን ነው የገለፀው፡፡

በአሁኑ ሰአት በአገሪቱ የ476 ሜጋ ዋት የሀይል እጥረት መከሰቱን የኢፌዴሪ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ አስታውቀዋል፡፡

በእጥረቱ ምክንያትም የኤሌክትሪክ ሀይል በመላ አገሪቱ በፈረቃ እንደሚሆን ሚንስትሩ ያስታወቁ ሲሆን ከፍተኛ ሀይል የሚጠቀሙ ድርጅቶችም በፈረቃው ይካተታሉ  ተብሏል፡፡

የሃይል እጥረቱን ተከትሎ ግብረ ሃይል በማቋቋም አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ሌሎቹ ግድቦች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመነጩ እየተደረገ ሲሆን ግልገል ጊቤ ሶስትን ጨምሮ አነስተኛ የውሃ ይዘት ያላቸው ግድቦች ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲያመነጩ እየተደረገ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የህብረተሰቡን የሃይል ፍላጎት መሰረት በማድረግ ፈረቃዎቹ በሶስት የተከፈሉ ሲሆን ፈረቃዎቹም ከንጋት 11 እስከ ረፋድ 5 ሰዓት፤ ከረፋድ 5 እስከ ቀን 10 ሰዓት እንዲሁም ከቀን 10 እስከ ምሽት 4 ሰዓት በመሆን ተደልድሏል፡፡

ችግን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የምትልከውን የሃይል መጠን በከፊል የምትቀንስ ሲሆን ወደ ሱዳን የምትልከውን ሃይል ሙሉ በሙሉ የምታቋርጥ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በቂ ዝናብ የሚጥል ከሆነ ችግሩ ሊቃለል እንደሚችልም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡