ምክር ቤቱ በ2012 ረቂቅ በጀት ላይ ተወያየ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ አመት የስራ ዘመን 43ኛ መደበኛ ስብሰባው በ2012 ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቷል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላለፈውን የ387 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት መግለጫ ለተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የበጀት ምደባው የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ፖሊሲ ትንበያዎችን መነሻ በማድረግ ነው የተደለደለ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ እድገቱን፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ፣ የሀገር ውስጥ ምርት እና ገቢን ለማሳግ የተያዘውን እቅድ መነሻ በማድረግ ነው፡፡

የበጀት ዝግጅቱ ዋና የፊሲካል ፖሊሲዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የእድገትና ትርንስፎርሜሽን እቅዱን መዳረሻና ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት አኳያ የድህነት ተኮር ሴክተሮችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የበጀት ድልድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ በጀቱ 387 ቢሊዮን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 289 ቢሊዮን ብሩ ከሀገር ውስጥ ገቢና በውጭ በእርዳታ ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን በዚህ አሀዝ መሰረት ከቀረበው ጥቅል በጀት ውስጥ የ97 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መኖሩ ተገልጿል፡፡

ይህን የበጀት ጉድለት በቀጥታ በጀት ድጋፍና በብድር ለመሸፈን መታቀዱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ንረት በማይፈጥር መልኩ የበጀት ምደባው መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

የ2012 በጀት ረቂቅ 387 ቢሊዮን ብር ሲሆን ከባለፈው የበጀት አመት የ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

ከአጠቃላይ የመደበኛ እና የካፒታል በጀት ውስጥ 63 ነጥብ 3 በመቶው ለመሰረተ ልማትና ማህበራዊ ተቋማት ግንባታ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

ይህም የበጀት ድልድሉ በዜጎች መካከል ያለውን የገቢ ልዩነት በማጥበብ ሀገራዊ የድህነት መጠኑን ለመቀነስና ለወጣቶች ሰፊ የስራ አድል በመፍጠር በሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

የሚኒስትሩን የረቂቅ በጀት ሪፖርት መግለጫ ያዳመጡት የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በተለይም ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከዋጋ ንረት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በመሰብሰብ በኩል መወሰድ ያለባቸውን የኢኮኖሚ እርምጃዎች አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የበጀት ድልድሉ ከካፒታል የልማት ፕሮጀክቶችና የክልሎች የበጀት ምደባ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የፍሀዊነት ችግር መፍትሄ ሳያገኝ የበጀት ምደባው መካሄዱ ተገቢ አይደልም የሚል ሀሳብም ተነስቷል፡፡

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሀገሪቱ ፍትሀዊ የበጀት ድልድልና የመሰረተ ልማት ስርጭት ለመፍጠር እየተሰራ ቢሆንም ከበጀት ምደባው ጋር ተያይዞ የተጀመረው ጥናት ጊዜ ስለሚያስፈልገው ለጊዜው በነባሩ አሰራር የበጀት ድልድል መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በረቂቅ በጀቱ ላይ በሰፊው የተወያየው ምክር ቤቱ ረቂቅ በጀቱን ለዝርዝር እይታ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡