ሴክሬታሪያቱ የግብርና ምርምር ዉጤቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ

የግብርና ምርምር ምክር ቤት ሴክሬታሪያት በግብርና ዘርፍ የተሰሩ የምርምር ዉጤቶችን ተደራሽ በማድረግ ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ዉይይት አካሄደ፡፡

በዉይይቱ ላይ የግብርና ሚንስትሩን አቶ አቶ ዑመር ሁሴንን ጨምሮ ከ200 በላይ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ልማት ታሪክ ከ1950 ጀምሮ የምርምር ቴክኖሎጂዉ ለተጠቃሚ ማህበረሰብ መድረሱን ተከትሎ በስትራቴጂካዊ ምርቶች ከነበረዉ ሀገራዊ ምርታማነት መጠን ከ150 በመቶ ወደ 300 በመቶ ያደገ ሲሆን በዚህ ሂደት ዉስጥ ከ3ሺ በላይ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡

በሀገሪቱ  የግብርና ምርምር ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላትና ምርምር የሚያከናዉኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር ስራዎች ቢሰሩም የምርምር ስርአቱና የግብርናዉ ኢኮኖሚዉ በሚፈለገዉ  ደረጃ በማዘመንና ዉጤታማነትን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ በውይይቱ እየተሳተፉ ያሉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

በግብርናዉ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና አጠቃላይ ማዕቀፉን  ለማሻሻል የሚያስችሉ ምክረ-ሀሳቦችን እንዲሁም  የክልልና የፌዴራል የግብርና ምርምር ተቋማት የሚሰሯቸዉን  የምርምር ዉጤቶችን  በተደራጀ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል ስራ በቀጣይ መከናወን እንዳለበት ተገልጿል፡፡