በበጀት ዓመቱ ማብቂያ 9.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ይጠበቃል

በጀት ዓመቱ ማብቂያ 9.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ይጠበቃል 

ያለፉትን 11 ወራት የሥራ አፈፃፀም መሰረት በማድረግ በ2011 የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 9 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2011 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ  ሰኔ 24/2011 አቅርበዋል፡፡   

የኢኮኖሚ እቅድ አፈፃፀሙ በተያዘው በጀት አመት ኢኮኖሚው እንዲረጋጋና እንዲያገግም ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምክንያቶች እንዲስተካከሉ እና በሁሉም አቅጣጫ ኢኮኖሚዉ አስተማማኝ  እንዲሆን የተለያዩ የማሻያ ስራዎች ተከናዉነዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሪፖርታቸው፡፡

አገሪቷ ትከተለው በነበረው የልማት ፋይናንስ ችግርና ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቷ ባጋጠመው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት የአገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት ምጣኔ ከዓመት ዓመት ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ከ2008 እስከ 2010 በጀት ዓመት አማካይ የአኮኖሚ እድገቱ 8 ነጥብ 6 በመቶ የነበረ ቢሆንም የ2010ሩ በጀት ዓመት እድገት ግን ወደ 7 ነጥብ 7ዝቅ ማለቱን አንስተዋል።

በመጠናቀቅ ላይ ባለው የ2011 ዓ.ም የአገሪቷ ኢኮኖሚ የ 9ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደሚያሳይ የተገመተ መሆኑን ገልጸው፤ በዘንድረው ዓመት ከሸቀጦች ንግድ አፈጻጸም  ዝቅተኛ ከመሆኑ በስተቀር የአገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚው እድት ከፍላጎትና አቅርቦት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ አገግሟል ብለዋል።

በዚህም ኢኮኖሚው አጋጥሞት ከነበረው ስር የሰደደ መዋቅራዊ ችግር ተጽእኖ በማላቀቅ፤ ቀውስ ሳይፈጥር ወደ ቦታው ማደግ ወደሚያስችበት ሁኔታ መመለሱ ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል።

እንዲሁም በአገሩቷ አጠቃላይ የስራ አጥ ቁጥር ከ11 ሚሊየን በላይ እንደሆ እና በየዓመቱ ከ2ሚሊየን ያላነሰ የሰው ሃይል ወደ ስራ ፍለጋ ገበያ ይቀላቀላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

አብዛኛው የተፈጠረው የስራ እድልም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት  መሆኑን ገልጸው፤ ወደፊት በግሉ ዘርፍና የውጭ የስራ እድሎችን በመጠቀም ሰፊ የስራ አማራጮችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በዘንድሮው ዓመት የአገሪቷ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም በእቅድ ተይዞ ከነበረው አፈጻጸም አንጻር ሲታይ ተስፋ ሰጪ ውጤት ታይቶበታል ነው ያሉት።