የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2012 የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያየ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛው ልዩ ስብሰባ በ2012 የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ የፓርላማ አባላት ከበጀት ፍትሐዊነት፣ ከካፒታል ፕሮጀክቶች በጀት አመዳደብ፣ ከኑሮ ውድነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በበጀቱ ዙሪያ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ከመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ጋርም ተያይዞ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በዚህም የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማስመልከት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ መንግስት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ የተገለጸ ቢሆንም በዕቅድ መካተቱን አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከመንገድ ፕሮጀክቶች አንፃር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ አዳዲስ የሚሰሩ መንገዶች ፕሮጀክቱ ባልተዳረሰባቸው አከባቢዎች ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ከ171 በላይ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ሀገሪቱ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ከፕሮጀክቱ መጓተት ጋር ተያይዞ ማጣቷን ገልጸዋል፡፡

ከአየር መንገድ ማስፋፋት ጋር ተያይዞ በበጀት አልተደገፉም የሚል ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ የአየር መንገዱ ትርፋማ በመሆኑና ያለውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት በመጠቀም ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ አካላት ድጋፉን በማግኘት እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በሀገሪቱ አምስት የአየር ማረፊያዎችን ለመስራት መታቀዱን ተጠቁሟል፡፡  

የማህበራዊ ዘርፎችን በተመለከተ ትምሀርት፣ ጤና እና የታዳጊ ክልሎች ድጋፍን በማስመልከት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው አቶ አህመድ ሽዴ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግስት የ2012 በጀት 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 109 ቢሊየን 468 ሚሊየን 582 ሺህ 456 ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ቢሊየን 710 ሚሊየን፣ 876 ሺህ 568 ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 140 ቢሊየን 775 ሚሊየን 506 ሺህ 265 ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፅሚያ ድጋፍ 6 ቢሊየን ብር እንዲሆን ነው ውሳኔ ያሳለፈው።