ኮሚሽኑ አዲስ የኢንቨስትመንት ህግ ሊያዘጋጅ መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አዲስ የኢንቨስትመንት አዋጅ በማዘጋጀት የህግ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ወራት ግብረ ሀይል በማቋቋም አዲስና ዘመናዊ ህግ ለማሻሻል ሲሰራ መቆየቱን አመልክቷል፡፡

የኢንቨስትመንት ህግ ማሻሻያ አላማው የሀገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ እና አዲስ እውቀት እና ቴክኖሎጅን መሳብ የሚያስችል አሰራርን ለመዘርጋት መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ገልፀዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ህጉ መሻሻል መንግስት እየተገበረ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያግዝ እና የተቀላጠፈ አሰራርን ለማምጣት እና ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተገልጿል፡፡

አዲሱ የኢንቨስትመንት አዋጅ በሀገሪቱ የሚገኘዉን ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥ ቁጥር የሚቀንስ እንደሆነም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡