ከግንቦት ወር ጀምሮ ለተከታታይ አራት ወራት በሚቀጥለው የክረምት የችግኝ ተከላ መረሃግብር 1 ነጥብ 39 ቢሊየን ችግኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መተከላቸው ተገለጸ፡፡
ፕሮግራሙን ለማስፈፀም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተቋቋመውና በሚኒስትሮች የሚመራው ኮሚቴ እስከአሁን የተከናወነውን ሥራና ዝግጅቱን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በዘንድሮ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ እስካሁንም 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውንም ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ከተሞችን ጨምሮ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክልሎች በሚከናወነው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከ760 ሚሊየን በላይ ችግኞች በከተሞች ይተከላልም ነው የተባለው፡፡
አስካሁን በተሰራው የተከላ ፕሮግራም በኦሮሚያ ክልል 470 ሚሊየን፣ በደቡብ ክልል 641 ነጥብ 9 ሚሊየን፣ በአማራ 280 ሚሊየን ኢንዲሁም በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ በርካታ ችግኞች መተከላቸው ተገልጿል፡፡
በቀጣይ ሐምሌ 22፤ 2011 ዓ.ም በአንድ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያሉ የዲፕሎማትክ ማህበረሰብ አባላት፣ አምባሳደሮችና የውጭ ሀገራት ዜጎች ተሣታፊ እንደሚሆኑም ታውቋል፡፡
የስነ ምህዳራዊና ኢኮኖሚያዊው ፋይዳው ከፍተኛ ነው በተባለው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ሁሉም የህብረተሰብ አካላት ተሣታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል፡፡
ከችግኝ ተከላው በዘለለም በቀጣይ ችግኞቹ ጸድቀው ለአየር ለውጥ ንብረትና ለደን ሽፋን መጨመር የሚኖራቸው አበርክቶ ከፍተኛ እንዲሆን ዜጎች የሚተክሉትን ችግኞች በዘላቂነት እንዲያንከባክቡም ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስትም ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር በተለየ ለሚተከሉት ችግኞች ዘላቂ ጥበቃ ያደርጋልም ነው የተባለው፡፡