የዘንድሮ በጀት ከቁጥሩ ባሻገር ታሞ የነበረው የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ማገገሙን እንደሚያሳይ ተገለጸ

የኢፌዴሪ መንግስት የ2012 ዓ.ም በጀት ከቁጥር ባሻገር ታሞ የነበረው የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ማገገሙን እንደሚያሳይ የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት በጀቱን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡበት ማብራሪያ ነው።

የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የ2012 ዓ.ም የመንግስት በጀት 386 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እንዲሆን ያጸደቀ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 34 በመቶ የሚሆነው ለካፒታል ወጪ የሚውል ነው።

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ እድገት በኣመዛኙ በመንግስት ወጪ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶት እንደነበር ዶክተር እዩብ ተካልኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያለባት የእዳ ክምችት ከአገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ከአስር ዓመት በፊት ከነበረበት 10 በመቶ ወደ 31 በመቶ ከፍ ማለቱን ደግሞ በአስረጂነት አንስተዋል።

ከፍተኛ የሆነ ውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የገቢና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን ለማክሮ ኢኮኖሚው ተጨማሪ ማነቆ እንደነበርም አብራርተዋል።

የችግሩ ጥልቀት መንግስት ባሳለፍነው በጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮክቶችን እንዳይጀምር አስገድዶት ነበር ነው ያሉት ዶክተር እዮብ።

ባለፈው አንድ ዓመት ኢኮኖሚው ላይ የተተበተቡ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የማደግ አቅም መጠቀም የሚያስችሉ ሪፎርሞች መተግበራቸውን ገልጸው፤ “ማሻሻያውም ከወዲሁ ፍሬ እያፈራ ነው” ብለዋል፤ ኢትዮጵያ በዓመቱ የ9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንዳስመዘገበች በመጠቆም።

በጸደቀው በጀት አዳዲስ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መያዛቸውን ለአብነት አንስተው፤ የገቢ ግብር አሰባሰቡን ለማሳደግ ከፍተኛ ስራ እንደሚሰራ አውስተዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባዬሁ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስራን በቀላሉ መከወን የማያስችሉ 80 ጠቋሚ ማነቆዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።

“ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ ያህሉ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፤” ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ዜጎች ተንቀሳቃሽ ኃብትን በማስያዝ በቀላሉ ብድር አግኝተው ወደ ስራ የሚገቡበት አሰራር መፈጠሩ ከማሻሻያው አንዱ መሆኑን በመጠቆም።

የአሰራር ማነቆዎች መፈታት የግሉ ዘርፍ ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጥር እንደሚያደርገው ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል። (ምንጭ፦ኢዜአ)