በኢትዮጵያ የፈጠራ ስራዎችን ለመደገፍ የሚውል የ100 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተደረገ

በኢትዮጵያ የፈጠራ ስራዎችን ለመደገፍ የሚውል የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ግብረ ሰናይ ድርጅት ካሊፍ ፎር ዴቨሎፕመንት ኢንተርፕራይዝ የተገኘ ነው።

ስምምነቱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በካሊፍ ፎር ዴቨሎፕመንት ኢንተርፕራይዝ የቦርድ ሰብሳቢ ሁሴን ጄዚም ኤል ናሁስ መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተፈርሟል።

በግብረ ሰናይ ድርጅቱ የተደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ በፈጠራ ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ድጋፍ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢንጂነር መኩሪያ በስምምነቱ የተገኘው ድጋፍ ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል ክትትል እንደሚያደርግና በአግባቡ ስራ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል።

አሁን ላይ በአገሪቱ የተጀመሩ የኢኖቬሽን ስራዎችን ለማጎልበት ድጋፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ከስምምነቱ በኋላም የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ልዑካን አባት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ችግኞችን ተክለዋል።