የፈረንሳይ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

የፈረንሳይ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ሊሜር የፊታችን ሰኞ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።

የሚኒስትሩ ጉብኝት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጋቢት 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ተከታይ መሆኑን ከፈረንሳይ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የፈረንሳይ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ሊሜር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ጋር እንደሚወያዩ ተጠቁሟል።

ውይይቱ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አገራቱ በተለያዩ ዘርፎች የተፈራረመችውን ስምምነቶች መተግበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ እንደሚያተኩር ኤምባሲው በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኢምባሲ አስታውቋል።

ብሩኖ ሊሜር ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሚጉበኙም ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ኢምባሲን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡