ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ንግድን ለማሳለጥ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ንግድን ለማሳለጥ ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ባለፉት ጥቂት ወራት በሀገሪቱ የተከናወኑ የተለያዩ ንግድ እንቅስቃሴዎችን መገምገማቸው ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም የሀገሪቱን የንግድ ዘርፍ እንቅስቃሴ ለማሳደግ በተቀመጡ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ የተካሄዱና ሊካሄዱ በሚገባቸው ማሻሻያዎች ዙሪያ መክረዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት እና ስራን በቀላሉ ለመጀመር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተጀመረው ስራ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ተናግረዋል።

ይህም ሀገሪቱ በምትስበው ኢንቨስትመንት እና ኢንቨስትመንቱ በሚፈጥረው የስራ ዕድል ልክ እንዲሁም ስራን በቀላሉ ለመጀመር ባለው ምቹነት ይመዘናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን በአሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 ላይ ለኢንቨስትመንትና ስራን በቀላሉ ለመጀመር ምርጥ ከተባሉ 100 ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ መሰረትም በአጭር ጊዜ ዕቅድ ውስጥ ባለፉት 6 ወራት ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራትን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ አብራርተዋል።

አቶ አበበ በማብራሪያቸው ባለፉት ስድስት ወራት የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅን በማሻሻል የአድራሻ ውል እና የንግድ ስምን የሚጠይቀው አሰራር ሙሉ በሙሉ እንዲቀር መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም የንግድ ምዝገባና ፍቃድ በኦን ላይን እንዲከናወን የማድረግ ስራ መጀመሩን አንስተዋል።

ባንኮች ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዘው እንዲበደሩ የሚያስችለው አዋጅ መውጣቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ሃብት ምዝገባን በተመለከተ ከፍተኛ መሻሻሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ የኢንቨስትመንትና የስራ ምቹነትን የሚያሳልጡ 8 ሕጎች እንደ አዲስ ረቀው መጽደቃቸውንና 40 አስተዳደራዊ ማሻሻያዎች መተግበራቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስ እንዲተገበሩ የተያዙት ዕቅዶችም አብዛኛዎቹ ተከናውነዋል ነው የተባለው ።

በሌላ በኩል እስከ ቀጣዩ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ የሚተገበሩ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅዶች በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርገዋል፡፡

ከንግድ ፍቃድና ምዝገባ ጋር በተያያዘ ሙሉ በሙሉ በኦንላይን አገልግሎት እንዲሰጥ፣ ብሔራዊ ባንክም የጸደቀውን አዋጅ ሙሉ በሙሉ እንዲተገብርና የተበዳሪዎችን ዝርዝር በዳታ ቤዙ እንዲያወጣ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘም ሃይል ፈላጊዎች ኦንላይን መጠየቅ የሚችሉበትና የጥገና ስራ በጂ አይ ኤስ ክትትል እንዲደረግ እንዲሁም ኃይል ጠይቆ ለማግኘት የሚፈጀው 60 ቀናት በ75 በመቶ እንዲቀንስ እቅድ ተይዟል።

ከገቢዎች አንጻርም ካሽ ሬጂስተር ማሽን ሙሉ በሙሉ ቀርቶ በሶፍትዌር እንዲተካና ግብር ከፋዮች ኦንላይን ግብር መክፈል እና ፋይላቸውን መከታል እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈ 30 በመቶ ግብር ከፋዮች ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ግብራቸውን እንዲከፍሉ የማድረግ ዕቅድም ተቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ በመካከለኛ ጊዜ ለኢንቨስትመንት እና በቀላሉ ስራ ለመፍጠር የሚያስችሉ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ ኢንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ መረጃው የኤፍቢሲ ነው፡፡