ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና እንዱስትሪ ቢሮ ከሌሎች ሴክተር ተቋማት ጋር በመሆን በቅርቡ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና እንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የንግድ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መስፍን አሰፋ እንደገለጹት፣ ከነጋዴ ህብረተሰብ ክፍል ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር የውይይት መድረኮች መደረጋቸውንና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ሱቆች፣ዳቦ ቤቶች፣ወፍጮ፣ የእህል መነገጃ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች እንደሚገኙበት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ዋጋ የጨመሩ፣ ያለ ደረሰኝ ግብይት የፈጸሙ፣ ግራም ያጎደሉና በተለያዩ መንገዶች በህብረተሰቡ ላይ ጫና ያደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስደዋል ብለዋል ኃላፊው፡፡

በተወሰደ እርምጃም መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውንና አልፈው አልፈው ከዚህ በፊት ከነበሩበት ዋጋ በታች የሆነበት አግባብም እንዳለ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በምርትና በሽያጭ ሂደት ውስጥ ምንም እሴት የማይጨምሩ ነገር ግን በህገ ወጥ መልኩ በገበያ ስርዓቱ ውስጥ የተሰገሰጉ ደላሎችን በማስወገድ ህብረተሰቡ በቀጥታ ከገበሬ ምርቱን ማግኘት እንዲችል ከተለያዩ ክልሎች ጋር በተለይም ከኦሮሚያ፣ከአማራና ከደቡብ ክልል ጋር እየሰራ መሆኑንም አቶ መስፍን መግለፃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡