ሐምሌ 22 በአዲስ አበባ 3 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል

ሐምሌ 22 በአዲስ አበባ ከተማ የሶስት ሚሊየን ችግኞች ተከላ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡

ዛሬ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት የአረንጓዴ አሻራ የንቅናቄ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቅናቄ መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ከተማ አስተዳደሩ በዚህ የአንድ አመት ጉዞው ካከናወናቸው በርካታ ተግባራቶች ውስጥ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ዋነኞቹ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ በተለይ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ለተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ማሰባሰብ እንዲሁም የችግኝ ተከላ ተግባራት መልካም ውጤት የታየባቸው ናቸው ብለዋል፡፡   

ምክትል ከንቲባው አያይዘውም እንደገፁት ሐምሌ 22 በአገራቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ በአዲስ አበባ ደረጃ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ችግኞች እንደሚተከሉና ለዚህም የሚሆን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ጉድጓዶች መቆፈራቸውንና ቀሪዎቹ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናቶች ውስጥ እንደሚጠናቀቁም ነው የተናገሩት።

ሐምሌ 22 በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ይሆን ዘንድ ከተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች የተውጣጡ ተወካዮች ከምክትል ከንቲባው እጅ ችግኞች ተረክበዋል።   

ትላንት “ለምለሚቱ ኢትዮጵያ” ትባል ነበር ያም የሆነው ትላንት አባቶች መሰዋእት ሆነው ሀገሪቱን ለዛሬዎቹ ትውልዶች ስላቆዩ መሆኑን የገለፁት ከንቲባው፣ ዛሬ እና ነገን መልካም ለማድረግ ልዩነታችንን ትተን አንድ በመሆን የተጣለብንን ኃላፊት ልንወጣ ይገባናል ሲሉም ለመላው የከተማዋ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።