የ2012 ዕድገት የሚለካው ሰውን ሥራ በማስያዝ መሆን እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር ዐብይ አህመድ ከዚ በኋላ የሚፈጠሩ ሥራዎችን በስም ሳይቀር በመዘርዘር ለምክር ቤቱ ተጨባጭ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ተናገሩ፡፡
ለሥራ ዕድል ፈጠራውም 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ከውጭ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ለዚሁ ሥራም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2012 ዓ.ም 3 ሚሊዮን የሥራ ዕድል የሚፈጥር የሠራተኛ እና ኢንቨስትመንት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
ኮሚቴው ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎችን በመፍጠር የሀገሪቱን ችግሮች እንደሚያቃልል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ከ10 ሚኒስትሮች ፣ ከ9 ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ከንቲባዎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኢንቨስትመንቱ ፈተና የሆነውን ሙስና፣ ቢሮክራሲ እና የኢንቨስተሮች አጋዥ ማጣት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሚገኙ ሲሆን፤ በየዓመቱ ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን የሥራ ፈላጊው ቁጥር እንደሚጨምር ተጠቁሟል፡፡
በ2012 ዓ.ም ብቻ ሊፈጠር ከታሰበው 3 ሚሊዮን ሥራ ውስጥ 1 ነጥብ 4 በጊዜያዊነት እና 1 ነጥብ 6 ደግሞ በቋሚነት ይፈጠራል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከዚህ በኋላ የሚፈጠሩ ሥራዎችን በስም ሳይቀር በመዘርዘር ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንደሚያቀርቡም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የ2012 በጀት ዓመት ዕድገት የሚለካው ሰውን ሥራ በማስያዝ እንደሆነ ሲል የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።