የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በኢትዮጵያ መጀመሪያ የሆነውን የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ በተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፍክ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ በሰጠት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የትራፍክ አደጋ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡
በተሽከርካሪዎች ለይ የሚገጠመው የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያው የተለያዩ ሀገራ ተሞክሮ ተወስዶ ተግባራዊ የተደረገ መሆኑንና የትራፍክ አደጋን ለመቀነስ እንደሚያስችል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ለሶስት ዓመታት ጥናት ተደርጎ ተግባራዊ የሆነው ቴክኖሎጂ አቅጣጫ ጠቋሚ (GPS)፣ ብሉቱዝ እንዲሁም ዩኤስቢን በመጠቀም ተቆጣጣሪውን በቀላሉ አሽከርካሪው በምን ያህል ፍጥነት እየተጓዘ እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ ለቁጥጥርና ክትትል አመቺ ነው ብለዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡
በመላ ሀገሪቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተሸከርካሪዎች ይኖራሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ በቀጣይ በሀገር ውስጥ ያሉት እንደሚገጠምላቸውና ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ደግሞ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያው ተገጥሞላቸው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የባለስልጣኑ 10 ተሸከርካሪዎች ላይ ቴክኖሎጂው የተገጠመ ሲሆን፣ በቀጣይ በሲኖትራክና የንግድ ተሸከርካሪዎች፣ የመንግስት መኪኖች እና የቤት መኪኖች ላይ በሶስት ደረጃዎች ተከፍሎ እንደሚገጠምም ተገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ስራ መሰራቱንም አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል፡፡