የግብርና ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት ለ1.3 ሚሊየን ዜጎች የገጠር ስራ ዕድል መፍጠሩን አስታወቀ

የግብርና ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት ለ1.3 ሚሊየን የገጠር ስራ ዕድል መፍጠሩን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2011 በጀት ዓመት በግብርና፣ በማዕድን ማናፋክቸሪንግ እና በሌሎች አገልግሎት ሰጪ መስኮች ላይ 1.8 ሚሊየን የገጠር ስራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ 1.3 ሚሊየኑን ማሳካቱን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የ2011 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀምና የ2012 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ እየተወያየ ሲሆን፣ በባለፈው በጀት ዓመት በገጠር የስራአጥነት ችግርን ለመቅረፍ በተሰራው ስራ የእቅዱን 73 በመቶ ማሳካት አሳክቻለሁ ብሏል፡፡

በዞን፣ ወረዳና ቀበሌ የአደረጃጀት እርከኖች ላይ የገጠር የስራ ዕድል ፈጠራ ባለቤት ማጣት በዘርፉ የሚታይ ዋነኛ ተግዳሮት እንደነበር  በውይይቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፤ የአቅም ማነስ፣ ተደራሽ የሆነ የመረጃ አያያዝ ችግር፣ የገበያ ትስስር ማጣት እንዲሁም የባለድርሻ አካላት በቅንጅት አለመስራት በማነቆነት ተለይቷል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት የኦሮሚያ ክልል የዕቅዱን 83 በመቶ፣ የአማራ ክልል ደግሞ 81 በመቶ በማሳካት የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ነበሩ ተብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተግዳሮትነት የተመዘገቡ ማነቆዎችን በማቃለል በ2012 በጀት ዓመት በመላ ሀገሪቱ 1.7 ሚሊየን የገጠር ስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ስራ ፈላጊዎች በፍላጎታቸው ወደ ስራ ከመግባት ይልቅ መንግስት ባስቀመጣቸው አማራጮች መሳተፋቸው በውጤታማነታቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸውም ገልጿል፡፡

በጥናቱ ከ2000 እስከ 2010 ዓ.ም በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ከ3.8 ሚሊዮን በላይ የስራ እድል እንደተፈጠረም ተመላክቷል፡፡