የመከላከያ ሰራዊትን ወታደራዊ እውቀት ለማሳደግ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠ/ሚኒስትር  ዐብይ አህመድ ገለፁ፡፡

የመከላከያ ሰራዊትን ወታደራዊ እውቀት ለማሳደግ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ገልፀዋል፡፡

የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 100 ከፍተኛ መኮንኖች ባስመረቀበት ወቅት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ከተመረቁት 100 ከፍተኛ መኮንኖች ውስጥ 92 ፖስት ስታፍ ሲሆኑ ስምንት ያህሉ የሁለተኛ ድግሪያቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም 21ዱ ከጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳንን የመጡ መሆናቸውም ነው በምረቃ ስነ ስርዓቱ ወቅት የተገለፀው።

የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ ለተመራቂዎች ዲፕሎማ በሰጡት ወቅት ሰልጣኞች በስነ ምግባር፣ በወታደራዊ ጥበብ፣ በሙያዊ ብቃትና በላቀ ዝግጅት የሰራዊት አባላትን ለመምራት የሚያስችላቸውን እውቀትና ከህሎት መከታተላቸውን ገልፀዋል።

በመሆኑም የቀሰሙትን ትምህርት ከዚህ በፊት ካገኙት ልምድና በተፈጥሮ ከያዙት  እውቀት ጋር በማዋሃድ በትጋት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊትን ወታደራዊ እውቀት ለማሳደግ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ እንደሚገኝም ነው የገለፁት፡፡

ወታደራዊ ተቋማት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ፣ በስነ ምግባር አርዓያዎች፣ ሀገርን እና ወገንን በመጠበቅ አኩሪዎች፣ ህግና ስርዓትን በማክበር እና በማስከበር ተምሳሌት መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።