በግንባታ ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል የወጡ ህጎች ባለመተግበራቸው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ በግንባታ ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል የወጡ ህጎች አለመተግበራቸው በሰራተኛው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከፍተኛ አድርጎታል ተብሏል፡፡

የህጎቹ በትክክል አለመተግበርም የግንባታ ባለቤቶች ለሰራተኛው ደህንነት መጠበቅ ትኩረት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል ነው የተባለው፡፡

ይህ የተባለው በአዲስ አበባ በተለይ በየካ፣ ቂርቆስ እና ቦሌ እንዲሁም የ20/80 እና የ40/60 የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በስፋት በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የጤና እና ግንባታ ደህንነት ላይ የተሰራ የህዝብ አስተያየት እና ጥናት ይፋ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡

የግንባታ ባለቤቶች የደህንነት ቁሳቁሶችን አለመጠቀማቸው እና የሚጠቀሙትም ቢሆኑ ርካሽ ዋጋን ፍለጋ ጥራታቸውን እና ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሳሪያዎችን ከውጭ አገር እያስገቡ ሰራተኛው እንዲጠቀምባቸው ማድረጋቸው በአዲስ አበባ ውስጥ በግንባታ ዘርፉ ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን ጉዳት ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

እንደ ኢቲቪ ዘገባ ዘርፉ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ850 ሺህ በላይ የስራ ዕድል የሚፈጥር ቢሆንም፤ ለዘርፉ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱና እና ደህንነቱን እንዲጠብቅ ባለመደረጉ በሰራተኛው ምርታማነት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተነግሯል፡፡