አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለመካፈል ወደ ዩጋንዳ አቀኑ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  በ3ኛው የኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለመካፈል ዛሬ ነሀሴ 09 ቀን 2011 ዓ.ም  ወደ ካምፓላ ተጉዘዋል።

ጉባኤው ከነሀሴ 8 ጀምሮ በካምፓላ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በፖለቲካ፣ በደህንነት፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ያደረጉ ሲሆን እነዚህን የትብብር ዘርፎች ለመተግበር የሚያስችል የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.ኤ.አ. ጁላይ 22 ቀን 2011 ተፈራርመው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ 

በትብብር ማዕቀፉ መሰረት ከዚህ ቀደም የመጀመሪያው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን በዩጋንዳ  ካምፓላ እንዲሁም ሁለተኛው በኢትዮጵያ አዲስ አበባ  ተካሂዷል። 
የአሁኑ  የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ደግሞ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በካምፓላ ለ3ኛ ጊዜ  በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በሁለቱ ሀገራት መሪዎች ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወደ ዩጋንዳእንዲሁም ከኡጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝቶች የተካሄዱ ሲሆን÷ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት አባል በሆኑባቸው ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ መድረኮች በመቀራረብና ተመሳሳይ አቋም በማራመድ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። 
በተለይም የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የትብብር ማዕቀፍ ሁለቱ ሀገራት ተቀራርበው እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለይተው በጋራ እንዲሰሩ አግዟል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በሚሳተፉበት በአሁኑ የ3ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የተለያዩ ስምምነቶች  ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ይፋዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1956 ዓ.ም ሲሆን ዩጋንዳ በ1962 ዓም ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች። 
ኢትዮጵያ በ1987 ዓም በቆንስላ ደረጃ በመክፈት በዓመቱ በ1988 ዓ.ም ወደ ኤምባሲ በማሳደግ ግንኙነቱን የማጠናከር ስራ መስራቷን ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው ዘገባ ያመለክታል፡፡