ኢትዮጵያ በኢንዶኔዢያ- አፍሪካ የመሰረተ ልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ እየተሳተፈች ነው

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የከተማ ልማትና ኮንስራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በባሊ ኢንዶኔዢያ በመካሄድ ላይ ባለው የኢንዶኔዢያ- አፍሪካ የመሰረተ ልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

በጉባዔው  በተካሄደው የፓናል ውይይት ማብራሪያ የሰጡት  ኢንጂነር አይሻ ባለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢከኖሚ ዕድገት ማሰመዝገቧን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በመሰረተ ልማት ልማት ያላትን ተሳትፎ ይበልጥ ውጤታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየሰራች መሆኗንም ገልፀዋል፡፡

በመንገድ መሰረተ ልማት ፣ በባቡር ሐዲድ ፣ በብሔራዊ ሎጅስቲክስ ልማት ፣ በትራንስፖርት ዘርፍና በአየር ትራንስፖርት ዘርፎች የተመዘገቡት ውጤቶች አስደናቂ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ለጉባኤው ተሳታፊዎች  አብራርተዋል፡፡

በተለይም  የኢትዮጵያ የባቡር ኮርፖሬሽኑ ዋና ከተማዋን ከጂቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኝ የ 656 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር መዘርጋቱንና ይህም ወደ ጅቡቲ ወደብ ለመድረስ ይፈጅ የነበረውን የ 84 ሰዓታት ቆይታ ጊዜ ወደ 10 ሰዓታት ድረስ ለመቀነስ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የግንኙነት ትስስርን እና መሠረተ ልማቶችን ለማጎልበት ብሎም የአካባቢያዊ ና የአለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማሳደግ የኢትዮ-ቴሌኮም ፣ የኢትዮጵያ የመርከብና የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉ በመንግስት የተያዙ ኩባንያዎችን በከፊል በግል ለማዞር የሚያችል ዕቅድ መዘርጋቱን ገልጸዋል ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከኢንዶኔዥያና ከህዝቧ ጋር በመሰረተ ልማትና በሌሎች ዘርፎች ለጋራ ብልፅግናና ልማት እንደምትሰራ መናገራቸውን ከኢፌዴሪ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢንዶኔዢያ- አፍሪካ የመሰረተ ልማት ጉባኤ በየዓመቱ ኤንዶኔዢያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትስሰስር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳየች ላይ የሚመክር ጉባኤ ነው፡፡