33 የምግብ አምራችና አስመጭዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በ33 የምግብ አምራችና አስመጪ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ የተቋሙን የ2011 እቅድ አፈፃፀም እና የ2012 እቅድ አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል።

የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሳምሶን አብርሃም እንደተናገሩት ህገ ወጥ ተግባራት ሲያከናውኑ በተገኙ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡

“ህገወጥ ተግባራትን በፈፀሙ አካላት ላይ ምርቶችን ከማስወገድ አንስቶ ተቋማቱን እስከ ማስዘጋት ደርሰናል” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ከዘርፉ የማስወጣት እና በህግ የመጠየቅ ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጡ ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ መድሃኒት እና ምግብ አስመጪዎች ላይ ፍተሻዎችን በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡

የታሸጉ ምግቦች በብዛት በበረሃማ አካባቢዎች ስለሚገቡ ወደ አደገኛ ኬሚካልነት እንደሚቀየሩና በኅብረተሰቡ ላይም ከፍተኛ የጤና ጉዳት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትሉ ተመላክቷል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ በበጀት ዓመቱ በኅብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሁም ድንገት በተደረገ ፍተሻ ከ4 ሺህ 763 ቶን በላይ ምግብ መያዙን አቶ ሳምሶን አስታውቀዋል።