የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሴት ሰራተኞች ተሳትፎ ለማሳደግ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዓለም ባንክ ድጋፍ የሴት ሰራተኞች ተሳትፎን ለመጨመር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ድጋፉ በተቋሙ የሚገኙ ሴት ሰራተኞች በቴክኒክና ሙያ፣ በኢንጂነሪንግና ሌሎች መስኮች ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

በ2025 ዓ.ም. የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ብርሃን ለሁሉ የተባለ ሃገራዊ ፕሮግራም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው፡፡

ለዚሁ ፕሮግራም ስኬታማነት ፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድርጅቱ ሴት ሰራተኞችን አቅም እና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በድርጅቱ ከሚገኙ ሰራተኞች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚረዳ ድጋፍ ከአለም ባንክ ያገኘ ሲሆን ለ5 ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

የሴቶችን አቅም ለማጎልበትም የዓለም ባንክ በየአመቱ የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ሴቶችን ማብቃት የአንድ ሴክተር ስራ መሆን ብቻ እንደማይገባው ገልፀዋል፡፡

ለተከታታይ አራት ዓመታት በየዓመቱ 40 ሴት ሰራተኞችን በቋሚነት በመቅጠር ድጋፉን እንደሚያጠናክር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡