ኮሪያውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለዉ ለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጠየቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴዑል የኮሪያ ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረምን የከፈቱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቀት በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ሂደት የውጭ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ገብተው መስራት እንዲችሉ የኢንቨስትመንት ህጉን ቀላል መደረጉን በመጠቆም፤ይህንን አጋጣሚ ኮሪያዊውያን ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ የተጀመረው የኢትዮጵያ ኮሪያ ቢዝነስ ፎረም በኮሪያ አፍሪካ ንግድ ማህበርና ፋዉንዴሽን በትብብር የተዘጋጀ ነው።

የኮሪያ አፍሪካ ፋውንዴሽን ኘሬዚዳንት በበኩላቸው፤ ኮሪያ የኢትዮጵያን ውለታ እንደማትዘነጋ ጠቅሰው ትብብራቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐብይ ከሀዩንዳይ ስራ አስፈፃሚ ሊ ወን ሂ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ ከኤል ጂ የኢኖቬሽን ጋለሪ ስራ አስፈፃሚ ስኮት አን ጋርም ተወያይተዋል።

ጋለሪውን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅቱ በኢትዮጵያ እያከናወነ ያለውን ማህበራዊ ሀላፊነት የመወጣት ተግባር አድንቀዋል።