ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ቁልፍ ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር እየሰራች ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንትና ባለሃብቶችን መሳብ በሚያስችል መልኩ ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

በጃፓን እየተካሄደ ባለው 7ኛው የቶኪዮ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ) ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ስለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ፣ ስለ ቀጠናዊ ውህደት እና በሃገሪቱ የተካሄዱ ማሻሻያዎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

 በንግግራቸውም በሁሉም ዘርፍ ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ ቅድሚያ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን በመጠቆም፤ በሁሉም ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጓን በመጥቀስ፤ የግሉ ዘርፍም ምርታማነትን በሚያሳድጉና ለስራ እድል ፈጠራ ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች የሚኖረው ተሳትፎ እንደሚቀጥልም አንስተው በዘርፉ የተደረገው ማሻሻያም ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

አሁን ላይም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ይስተዋሉ የነበሩ ተግዳሮቶች ማሻሻያ የተደረገባቸው መሆኑን ገልጸው፤ ለባለሃብቶች ተሳትፎ በሚያመች መልኩ የተንዛዙ አሰራሮችን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛን ለመጠበቅና ተከታታይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል መልኩ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ማድረጉን አስረድተዋል።

ማሻሻያዎቹ ፈጠራን እና የአፈጻጸም ብቃትን ማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ቀጠናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለእድገት በተለይም ተከታታይነት ያለውና ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚያዊ ውህደት በቀጠናው ለሚኖረው የሰላም ግንባታ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው እንረዳለንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ገበያን በመጠቀም ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት በግንባር ቀደምትነት ትሰራለችም ነው ያሉት።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጃፓን የአፍሪካን እድገት የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች ብለዋል፤ የትብብሩ ትኩረትም በኢንቨስትመንት እና ፈጠራ ላይ መሆኑን በመጥቀስ።

ባለፉት ሶስት አመታት የጃፓን ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱን ጠቅሰው፥ ቶኪዮ አሁን ላይ  በአህጉሪቱ በሠላም ሂደት እየሠራች መሆኑን አስታውሰዋል።

በጃፓኗ ዮኮሃማ መካሄድ የጀመረው ፎረሙ “የአፍሪካን ልማት በሰው ሃብት፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ ማራመድ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።