ጠንካራ እና ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ

የገንዘብ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ውስጥ ጠንካራ እና ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር የማሻሻያ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

28ኛው ዙር የፌደራልና የብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የፋይናንስና ገቢ ዘርፍ ምክክር መድረክ በገንዘብ ሚኒስቴር እየተካሄደ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በምክክር መድረኩ ላይ በሀገሪቱ ውስጥ ጠንካራ እና ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር በፌደራል እና በክልሎች የሚገኙ የፋይናንስና ገቢ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደርን ለማዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበው ገቢ ማደግ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልም የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር ተከታታይነትና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የገቢ ማደግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ በ2012 በጀት ዓመት ለግብር ከፋዩ ምቹና ቀልጣፋ የግብር አከፋፈል ስርአት እንዲኖር ለማስቻል እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

የምክክር መድረኩ የኮንትሮባንድ ንግድን መከላከልና ህገ-ወጥ ንግድን ከመቆጣጠር አንፃር እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ ተወያይቶ ጠንካራ የአሰራር ስልቶችን መንደፍ በሚቻልበት አግባብ ላይ በስፋት እንደሚወያይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።