በዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ በመጪው መስከረም ወር ቆጠራ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብርቅዬ የዱር እንስሳት በሆኑት ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ በመጪው መስከረም ወር ወቅታዊ የቆጠራ ሥራ እንደሚካሄድ የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የፓርኩ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በመጪው መስከረም ወር ላይ የሚካሄደው ወቅታዊ ቆጠራ ሁለተኛ ዙር ነው።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ቆጠራው የሚካሄደው ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና የቀይ ቀበሮ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ያሉበትን ሁኔታ አውቆ ክትትል ለማድረግ ነው።

የቆጠራ ሥራው በፓርኩ ክልልና አዋሳኝ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የሚካሄድ ሲሆን ይህም በተጨባጭ መረጃ ተመስርቶ ለጎብኚዎች መረጃ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

“ቆጠራው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፓርኩ ላይ ደርሶ በነበረው የእሳት አደጋ በዱር እንስሳቱ ላይ ጉዳት መድረሱንና አለመድረሱን በተጨባጭ ለማረጋገጥም ያግዛል” ተብሏል።

የዱር እንስሳቱን የውልደትና የሞት መጠን፣ የአመጋጋብ፣ የመኖሪያ አካባቢና ስርጭትን ለማወቅ እንዲሁም የሚደርሱ አደጋዎችን በመለየት ለቀጣይ ግብዓት ለመሰብሰብ እንደሚያስችልም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ አበባው ገለጻ ቆጠራውን ለማካሄድ የሚያስችሉ የቆጠራ ቦታዎች ልየታ የተካሄደ ሲሆን በእዚህም ከ130 በላይ የቆጠራ ቦታዎችም ተዘጋጅተዋል፡፡

ለቆጠራ ሥራው በዘርፉ ልምድ ያላቸው 150 ግለሰቦች መመልመላቸውንና ቆጠራውን በትክክል ማካሄድ እንዲችሉም በባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
የቆጠራ ስራው ለ15 ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ጂ.ፒ.ኤስ በተባለው አቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ በመታገዝ ጭምር የሚከናወን መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ለቆጠራው ስራው ከ380 ሺህ ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ ኃላፊው ጠቁመው “አፍሪካን ዋይልድ ፋውንዴሽን” የተባለ መግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በጀቱን ለመሸፈን ቃል መግባቱን ነው የተናገሩት፡፡

ባለፈው መጋቢት ወር የበጋ ወራት የዱር እንስሳት ቆጠራ በፓርኩ ውስጥ መካሄዱን ያስታወሱት ኃላፊው በቆጠራው ቀይ ቀበሮ 73፣ ዋልያ 619፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ደግሞ 18ሺህ 500 መገኘቱን ገልጸዋል፡፡