በአማራ ክልል በ150 ሚሊየን ብር ግንባታው የተከናወነው ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖሎጂ ተመረቀ

በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ የተገነባው ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖለጂ ኩባንያ በ150 ሚሊየን ብር የግንባታና የማሽን ተከላ ስራው ተጠናቆ ተመረቀ።

ኩባንያውየአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው እለት ተመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፥ ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖለጂ የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት የክልሉንና የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ በአካባቢው የሚገኝ ጥሬ እቃ የሚጠቀም በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖለጂ የስታዲየም በሮችን፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር እንዲሁም የመስኖ ማሽኖችን በማምረት የግብርናውን ትራንስፎርሜሽን እድገት እንደሚያፋጥን ገልፀዋል።

ርእስ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን አክለውም፥ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋዕኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።

ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖለጂ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያች አቶ አቻም ደምስ በበኩላቸው፥ ኩባንያው በክልሉ የልማት ድርጅቶች እና ጎልደን ትረስት ኩባንያ በአክሲዮን የተቋቋመ መሆኑን ገልፀዋል።

ኩባንያው ስራ ሲጀምር በ19 ሚሊየን ብር ካፒታል እንደነበረው በመግለፅም አሁን ላይ ካፒታሉን ከ244 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

የክልሉ የልማት ድርጅቶች ድርሻ 95 በመቶ መሆኑን በመግለፅ፥ ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖለጂ ኩባንያ የግንባታ እና የማሽን ተከላ ስራውን ለማከናወን 150 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

ኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖለጂ በ7 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያሰረፈ ሲሆን፥ ከ80 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በቋሚነት እንዲሆም  ከ150 በላይ ሰዎች በጊዜያዊነት የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል።

በቀን እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ልዩ ልዩ የፕላስቲክ ምርቶችን የማምረት አቅም እንዳለውምየኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አቻም ደምስ አስታውቀዋል። (አብመድ)