ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ለአፍሪካ ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ ገቡ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ለአፍሪካ 2019 ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ገብተዋል።

ፕሬዝዳንቷ ኬፕ ታውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አልቪን ቦትስ፣ በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያምና የኤምባሲው ዲፕሎማቶች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፎረሙ በፈረንጆቹ ከመስከረም 4 እስከ 6 ቀን ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፣ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ ሀገራት የተወከሉ ቁጥራቸው 1ሺህ 100 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በፎረሙ ታዳጊ የቢዝነስ ጅማሮዎችን በካፒታልና በፖሊሲ መደገፍ፣ የሰራተኞችን ክህሎት ማጎልበት እና ኢ-ኮሜርስን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶች ይካሄዳሉ።

ከዚህ ባለፈም አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በሚታገዙበት እና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተፈጻሚነት ዙሪያ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን ከደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።